Friday, July 4, 2014


ከዘመዶችህ ተለይተህ ውጣ።
ዘፍ. ፲፪፥፩


መግቢያ

ለክርስቲያኖች፣ ለሙስሊሞችና ለአይሁዶች አባቶች፥ የመጀመሪያ የሆነው አብርሃም፥ የቀድሞ  ስሙ፥ አብራም ነበረ፤ አብራም ማለትም፥ ታላቅ አባት ማለት ነው። ከታላቅ አባትነት፥ ወደ “የብዙዎች አባትነት”፥ በእግዚአብሔር ከመሾሙ በፊት፥ በትውልድ ሀገሩ በዑር፥ ከዘመዶቹ ጋር በአካልም፣ በምግባርም ይኖር ነበር፤ በኋላ ግን፥ እግዚአብሔር ዘራቸው እንደማይቆጠር የሰማይ ከዋክብት፥ የብዙ አህዛብ አባት ይሆን ዘንድ ሲያጨው፥ “ከአገርህ፣ ከዘመዶችህም፣ ከአባትህም ቤት ተለይተህ፥ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ።” አለው። ስሙንም፥ አብርሃም ብሎ ለወጠው። አብርሃምም፥ ጥሪውን ሲረዳና ከዘመዶቹ ተለይቶ  ሲወጣ፥ “የምድር ነገዶች ሁሉ በአንተ ይባረካሉ፤” የሚለው ተስፋ፥ በክርስቶስ እንዲፈጸም፥ የድኅነት ምክንያት ሆነ።  

ተለይቶ መውጣት

እግዚአብሔር የእርሱ እንዲሆኑና፥ በምድራችን የመልካም ነገር መገኛና፣ የበረከት ምንጭ እንዲሆኑ የሚፈልጋቸው ሰዎች፥ ተለይተው እንዲወጡ ይፈልጋል። ለዚህም ዋና ምክንያቱ፥ እግዚአብሔር በባሕርዩ ቅዱስና ንጹሕ ስለሆነ፥ የተደበላለቀና ተለይቶ  ያልጠራ ነገር ስለማይስማማው ነው። ለዚህ አመክንዮ  ማስረጃውም፥ በኦሪት ዘሌዋውያን፥ ፲፩፥ ፵፬ ላይ እንዲህ ሲል ይገኛል፦ “እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ፥ እኔ ቅዱስ ነኝና በምድርም ላይ በሚሳብ ተንቀሳቃሽ ሁሉ ሰውነታችሁን አታርክሱ።” በግዕዝ ቋንቋ፥ ቅዱስ ማለትም የተለየ ማለት ነው። ይልቁንም እግዚአብሔር፦ “እኔ እግዚአብሔር ቅዱስ ነኝና፥ ለእኔም ትሆኑ ዘንድ ከአሕዛብ ለይቻችኋለሁና ቅዱሳን ትሆኑልኛላችሁ።” ይላል። ዘሌ. ፳፥ ፳፮

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም፥ ሊከተሉት የሚወዱ ሁሉ፥ ከሌሎችና ከዘመዶቻቸው ብቻ ሳይሆን፥ ከራሳቸው ሀሳብም ጭምር ተለይተው መውጣት እንዳለባቸው አስተምሯል። ማቴ. ፲፮፥ ፳፬፣ ማር. ፰፥ ፴፬፣ ሉቃ. ፮፥ ፳፫። በአጠቃላይ፥ ቅዱሳን ተብለው የድል አክሊል የተቀዳጁ ሁሉ፥ ከዘመዶቻቸውና በወቅቱ ካለው አስተሳሰብና ኑሮ ተለይተው የወጡ ናቸው። ዕብ. ፲፩

ከምን መለየት?

ሰው ወይም ማንኛውም ነገር፥ ለእግዚአብሔር ሲለይ፥ ቅዱስ ይባላል።[1] በብሉይ ኪዳን፥ ሰው ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ ሲሆን፥ ሥርአት ይፈጸምለታል። በሐዲስ ኪዳን ግን፥ ሰው በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ፣ በዓለም ካለው ምድራዊ አስተሳሰብና ክህደት የተለየ ሲሆን፥ ቅዱስ ይባላል፤ በጠባዩና በምግባሩም የታወቀ ይሆናል። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን፥ ከእናትና  ከአባታቸው፣ ከሚስቶቻቸውም ተለይተው እንዲወጡ ጠይቋቸዋል። በጻድቅነትም፥ ከአይሁድና  ከፈሪሳዉያን አስተሳሰብ የተለየ ጽድቅ እንዲኖራቸው አሳስቧቸዋል። ማቴ. ፭፥ ፳

ክርስቲያን በተለይም፥ ከአስመሳይነት፣ ከዘረኝነት፣ ከዓላማ ቢስነት፣ ከትምክህተኝነት፣ ከትዕቢተኝነት፣ ከተሳዳቢነትና ከአሳዳጅነት መለየትና እግዚአብሔር ወዳዘጋጀው የሰማያዊ  ምሥጢር ልዕልና መውጣት አለበት። ይልቁንም፥ የአምልኮት መልክ እያላቸው ኃይሉን ግን ከካዱ ሰዎች መራቅና በምግባር ክእነዚህ ተለይተን መውጣት እንዳለብን  ቅዱስ ጳውሎስ በ፪ኛ ጢሞቴዎስ ም.፫ ያስገነዝበናል።

ተለይቶ አለመውጣት፣

በእግዚአብሔር ከተጠሩና ከተመረጡ በኋላ ተመሳስሎ መኖር፥ ብዙ ዋጋና አላስፈላጊ መስዋእትነትን ያስከፍላል። አብርሃም እግዚአብሔር እንዳዘዘው፥ ከዘመዶቹ  ተለይቶ ከመውጣት ይልቅ፥ ክአባቱና ከሎጥ ጋር ተዳብሎ መጓዝን መረጠ፤ ስለዚህ ወደ ተስፋይቱ  ምድር ወደ  ከነዓን የመድረሻውንና የተስፋውን ልጅ፥ይስሐቅን የመውለጃውን ጊዜ አራዘመው። እንዲሁም እኛ፥ በይሉኝታና በተለያዩ ማኅበራዊ መረቦች ተጠምደን፣ እውነትን ይዘን ሀሰትን ግን መቃወም ያቃተን፣ ሀገራችን በሰማይ ነው ብለን፥ ነገር ግን ከዘረኞች እርሾ ያልጸዳን፣ የስደተኞች መጠጊያ የሆነውን ክርስቶስን እየተከተልን፥ ሰዎችን ግን ከማሳደድ ያልታቀብን፥ መንገዳችንን ልንመረምር ይገባናል። ተመሳስሎ መኖርና ተለይቶ አለመውጣት፥ ብዙ ዋጋና አላስፈላጊ መስዋእትነትን ያስከፍላልና፥

ማጠቃለያ

ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ። ዘፍ. ፲፪፥፩

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


[1] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ  ቃላት፤ ገጽ ፺፯፣ ቅዱስ የሚለውን ይመልከቱ።

No comments:

Post a Comment