Sunday, October 19, 2014

Part Time Priests - ፓርት ታይም፥ ቄሶች


ፓርት ታይም ቄሶች

በመቅደስ ነገር የሚያገለግሉ፥ ከመቅደስ የሆነውን ነገርን እንዲመገቡ፣
በመሠዊያውም የሚጸኑ፥ ከመሠዊያው እንዲካፈሉ አታውቁምን?

፩ኛ ቆሮ. ፱፥ ፲፫

መግቢያ
ሰሞኑን በአንድ የአትላንታ ከተማ ነዋሪ በሆነ ወጣት የተደረሰች፥ “እሳትና  ውሃ” የተሰኘች መጣጥፍ አነበብኩኝ፤ ከመጽሐፉ ውስጥ፥ “እምነት” በሚል ርዕስ የተጻፈች ፥ አንዲት ስድ ንባብ የማንበብ ፍላጎቴን ሳበችውና አነበብኳት። በዚች ስድ ንባብ ውስጥ ከዋና ገጸ ባሕርያቱ ከተከስተና ከአባቱ  ከአቶ  ደጉ ፥ ይልቅ የሀልዮት ቀልቤን የሳቡት ገጸ ባሕርይ ፥ የፓርት ትይሙ ቄስ፥ ቄስ ፈለቀ ናቸው። ቄስ ፈለቀ የተሰጣቸውን ገጸ ባሕርይ ስመለከት፥ የአትላንታ ሕዝበ ክርስቲያን ለቀሳውስቱ  ያለውን እውነተኛ አመለካከት በጥቂቱም ቢሆን የሚያንጸባርቅ ሆኖ  አገኜሁት። ደራሲው፥ እንዲህ ዓይነት ገጸ ባሕርይን ለቄስ ፈለቀ ለምን አጕናጸፋቸው? ሳይሆን፣ እንዲህ ዓይነት ባሕርይን እንዴት ሊያጕናጸፋቸው ቻለ? ብዬ መጠየቄ አልቀረም። በእውነቱ እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ ከሥነ ጽሑፍ ገጸ ባሕርይነት ባሻገር በግልጽ ብንወያይበት፥ በሃይማኖታችን ውስጥ ላለብን ችግር መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል ብዬ አመንኩ። ስለዚህ የውይይቱን በር ለመክፈት፥ ይህችን ጽሑፍ ጻፍሁኝ። የዚህች ጽሑፍ ዓላማ፥ የውይይት መድረክ መክፈትና ፥ አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ፥ ከመሰዳደብ የዘለለ የጋራ መፍትሔ ነው የምንለውን ለመጠቋቆም ነው። ለመግባባት ይመች ዘንድ፥ ካህን በሚለው ቃል ፈንታ፥ ቄሶች የሚለውን የዕለት ተዕለት ቃል ተጠቅሜበታለሁ።

ለመሆኑ ቄሶች ለምን ፓርት ታይም ይሆናሉ? ለዚህ ውይይት በር የከፈተውን የ“እሳትና  ውሃ”ን ደራሲ፥ ወንድሜን ቴዎድሮስ ታደሰን እያመሰገንኩኝ፥ ቄሶች ለምን የ “ፓርት ታይም ቄሶች” እንደሚሆኑ፥ የበኩሌን ለምግለጥ እሞክራለሁ።

ቄስነት

ቄስ ወይም ቀሲስ፥ የሚለው ቃል ፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ፥ ካህን ወይም ሽማግሌ ከሚሉት ቃላት ጋር፥ በተለዋዋጭነት ያገለግላል። (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት; ገጽ ፻፺፪)። የሚያስተላልፈው ጽንሰ  ሃሳብም ፥ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ሆኖ፣ ሰውን ከእግዚአብሔር ጋር ማገናኜትንና፥ የእግዚአብሔርን ምሕረት ለሰው ማስተላለፍን ነው።  አገልግሎቱም ፦ ከሰው ወደ  እግዚአብሔር መስዋዕት በማቅረብና፣ ከእግዚአብሔር ወደሰውም፥ የኃጢአት ስርየትንና ይቅርታን በማስገኘት ይፈጸማል። ስለዚህ፥ ቄስነት በራሱ ሳይሆን፥ ልክ እንደውሃ ማስተላለፊያ ቧንቧ፥ በሚሰጠው አገልግሎትና ጥቅም ብቻ የሚገለጽ፥ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።

ቄስ፥ በማንኛውም ሃይማኖት ውስጥ አለ። በሦስቱ ዋና ሃይማኖቶች፥ ሕግ በሙሴ በኩል ለሰው ከመሰጠቱ በፊት ፥ እያንዳንዱ የቤተሰብ መሪ፥ ለቤተሰቡ ቄስ ነበረ። ዘፍ.፬፥፫ ፣ ዘፍ. ፰፥፳፣ ዘፍ. ፲፪ ። እግዚአብሔር ሕግን ለሙሴ ሲሰጥ ግን ፥ አሮንና ልጆቹ፣ ከዚያም በኋላ ሌዊና፡ ዘሩ ቄሶች እንዲሆኑ ተመረጡ፤ ዘጸ. ፳፰፣ ዘኍ. ፫። እንግዲህ እነዚህ ዘሮች፥ የሙሉ ሰዐት ቄሶች ሆነው እያገለገሉ ፥ (የፉል ታይም ቄስነት)መሠረት፥ በዚሁ ተጣለ። እግዚአብሔር ራሱ ከገለጸላቸው ትቂት ቅዱሳን ሰዎች በስተቀር ፥ የብሉይ ኪዳን ቄስነት፥ በመወለድ ላይ የተመሠረተ ነበር።

በሐዲስ ኪዳን ፥ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፥ ራሱን መስዋዕት፣ ራሱን መስዋዕት አቅራቢ  ካህንና፥ መስዋዕት ተቀባይ ጌታ፥ አድርጎ ፥ በመለኮታዊ ምሥጢሩ  መስዋዕት አቅርቧልና፥ የመወለድንና በዘር ብቻ የሚገኝን ቄስነት አስቀረ። ዕብ. ፯። ስለዚህ በሐዲስ ኪዳን፥ መንፈሳዊ የሕይወት መዓዛን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ሁሉ በአጠቃላይና፣ በተለይም በሚሰጡት አገልግሎት ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሱ፥ የተመረጡ መንፈሳውያን አገልጋዮች፥ ቄሶች ተባሉ። ዕብ. ፲፥ ፲፱-፳፭፣ ፩ኛ ጢሞ. ፫። ነገር ግን፥ የእያንዳንዱ ሰው የጸጋ ሥጦታ የተለያየ በመሆኑ፥ ማኅበሩ  ተጠቃሚ  ይሆን ዘንድ፥ አገልጋዮች የተለየ መንፈሳዊነት፣ አኗኗር ፣ ትምህርትና አመራር እንዲኖራቸው፥ ቄስነት ራሱን የቻለ ሞያና ዘርፍ እንዲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ተደነገገ። ሐዋ. ፮፥፩-፮

የቄስ ሙያ/የሥራ ድርሻ፤

ቄሶች አገልግሎታቸውን በላቀ ጥንቃቄና ውስጣዊ ንጽሕና እንዲፈጽሙ ታዘዋል። ከብዙ በትቂቱ፥ የቄስ የሥራ ድርሻ፥ የሚከተሉትን ያካተተ  ነው፦
1. በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ማገልገልና መላላክ፤ ዘኍ. ፲፮ ፥፵
2. የእግዚአብሔርን ሕግ፥ በየጊዜው መማርና ለሕዝቡ ማስተማር፤ ሕዝ.፯፥፳፮፣ ሮሜ ፪፥ ፳፩
3. ለታመሙትና ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ መጸለይ፤ ያዕ. ፭፥
4. በፍቅር መስራትና ፣ ፍቅርን ለሕዝቡ ሁሉ መስበክ፤ ፩ኛ ተሰ. ፭ ፥፲፪
5. የተጣሉትን ማስታረቅና፥ በመንፈሳዊ  ሰዎች ላይ ፍትሕና ዳኝነት መስጠት፤ ፩ኛ ቆሮ. ፭
6. የተረሱትንና አስታዋሽ የሌላቸውን መጎብኜት፤ ፩ኛ ጢሞ. ፭
7. ምክር መስጠት ናቸው።

እንግዲህ የቄስ ሥራ እነዚህና የመሳሰሉት ሲሆኑ፥ እነዚህን ሥራዎች ለመስራት ግን፥ የእግዚአብሔር ፈቃድና የምዕመናን/እውነተኛ አማኞች ይሁንታ ያስፈልጋል። ለዚህም ነው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፮ እንደዚህ የሚለን ፦
“ወንድሞች ሆይ፥ በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፥ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን፤”

ፓርት ታይም ቄሶች

በመሠረቱ የክርስትና ሃይማኖት የመጀመሪያ ዘመን ቄሶች፥ ፓርት ታይም ቄሶች ነበሩ ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ቅዱስ ጳውሎስ፥ ቀን ሲሰብክ እየዋለ፥ ማታ ማታ ድንኳን ይሰፋ፣ የተቸገሩትንም በገንዘቡ ይረዳ ነበር። ሐዋ. ፲፰። እነ ቅዱስ ሉቃስ ሀኪሞች፣ እነ ዲዮስቆሮስም ጠበቆች፥ እንደነበሩ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል። ሆኖም፥ ቤተ ክርስቲያን እያደገች ስትሄድ፥ ሥራው ሙሉ ጊዜን የሚጠይቅ እየሆነ ሄደ። ስለዚህ፥ የቅስና ሥራ በአግባቡ ሲሰራ፥ ብዙ  ትምህርትን፣ ጊዜንና ጉልበትን የሚጠይቅ በመሆኑ፥ በጊዜ  ሂደት ቅስና የሙሉ ሰዐት ሞያ ወደ መሆን ተሸጋገረ።
የቄስ ሥራ፥ እንደ  ቅዱሳት መጻሕፍት ሃሳብ በአግባቡ ከተሰራ፥ በፓርት ታይም የሚታሰብ ሥራ አልሆነም፤ ማለትም፥ ቄሱ፦ ለማስተማር መጻሕፍትን ማንበብና መመርመር አለበት፤ ቄሱ፦ የታሰሩትንና የታመሙትን ለመጎብኜት ጊዜና ገንዘብ ያስፈልገዋል፤ በንስሐ የሚመለሱትን ተስፋ ለማሳየት፥ ተነሳህያኑ በፈለጉት ጊዜ ሊያገኙት ይገባል፤ ቄሱ፦ የእግዚአብሔርን ምሕረት ለሕዝቡ ለማስተላለፍና፣ የሕዝቡንም ምልጃ ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብ፥ ራሱ ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኝበት የጸሎትና የንስሐ ጊዜ፥ የግድ ሊኖረው ይገባል። ከነዚህና፥ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም ከሚፈልገው ጥንቃቄ የተነሳ፥ በአብዛኛው የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ፥ በተለይም በካቶሊክ፣ በፕሮቴስታንትና እንደ ግብጽ ባሉ ኦርቶዶክሶች፥ ቄሶች የሙሉ ሰዐት አገልጋዮች ናቸው። ፓርት ታይም ቄሶች የሚባሉም አይታወቁም። ዳሩ ግን፥ አንድ ሰው የምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ተጠቃሚ ካልሆነ በስተቀር፥ ይህንን እውነታ ለመረዳት፥ ሊቸገር እንደሚችል አያጠራጥርም።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ፥ ፓርት ታይም ቄሶች በአሜሪካ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ የራሷ የሆነ መልክ፣ ባሕልና ውበት ያላት ድንቅ ቤተ ክርስቲያን ናት። እስከ 1960ዎቹ መጨረሻ ድረስ፥ ብዙም ወደ ምዕራቡ ዓለም የመሰደድ ችግር/አጋጣሚ አልደረሰባትም። ሆኖም ልጆቿ በትምህርትም ሆነ በፖለቲካ ምክንያት ሲሰደዱና በሄዱበት ሲቀሩ፥ እርሷም አብራቸው ተሰደደች።

ስደት የራሱ የሆነ፥ መልካምም ሆነ ክፉ ገጽታና ተጽዕኖ አለው። ለጸኑትና እምነታቸውን ከሌላ የሕይወት ዘርፍ ላላቀላቀሉ ክርስቲያኖች፥ ስደት አማራጭ ያልተገኘለት የመስፋፊያና ከእግዚአብሔር ዘንድ የሕይወት አክሊልን የመቀዳጃ መንገድ ነው። ሐዋ. ፮፣ ፯፣ ፰።

ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ሮሜ ፰፥ ፴፭

በሌላ መልኩ፥ በአምነታቸው ላልጕለበቱና፥ ሁልጊዜ የቃልን ወተት እየተመገቡ፣ ሳያድጉ መኖርን ለለመዱ አማኞች፥ ስደት መጥፊያቸው ብቻ ሳይሆን፥ ሌላውንም ጨምረው የሚያጠፉበት ጉልበታቸው መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ። ፩ኛ ጴጥ. ፬።

አሜሪካ በምትገኜው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፥ የ “ፓርት ታይም ቄሶች” እንዲፈጠሩ ካደረጉ ምክንያትች ዋናው፥ ስደት ነው። ...
ይቆየንና በሚቀጥለው ዕትም፥ እንቀጥለዋለን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር!
ቀሲስ ማንችሎት ገበየሁ፤
የአትላንታ ፈለገ ጥበብ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን፥ ካህን፤

No comments:

Post a Comment