Thursday, May 22, 2014

የእግዚአብሔር ሰላም/ God's Peace


የእግዚአብሔር ሰላም

“አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ፥ የእግዚአብሔር ሰላም ፦
ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።
 ፊል. ፬፥ ፯


መግቢያ፤
ሰዎች ሲገናኙ የሚለዋወጡት የንግግር መክፈቻ ቃል ከመሆኑ ባሻገር፥ ሰላም በሰዎችና በፍጥረት መካከል፥  ስምምነት ሲኖር፣ የሚፈጠር አንድነትና ዕረፍት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፥ ከ፫፻ ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። በኃጢአት ምክንያት፥ በሰዎችና በእግዚአብሔር መካከል የጥል ግድግዳ በነበረበት በብሉይ ዘመን፥ ሰላም ከሰዎች ርቆ ነበር። ይሁንና፥ ከእግዚአብሔር ጋር የሰመረ ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች፥ ሰላም ባልነበረበት በዚያ ዘመን እንኳ፥ ለራሳቸው ሰላም እንደነበራቸው ገልጸዋል። ለአብነትም ያህል፥ ቅዱስ ዳዊት፥ “ሰላምን ከሚጠሉ ጋር ነፍሴ ብዙ ጊዜ ኖረች።” በማለት፥ ግላዊ ሰላምን ጠብቆ መኖር እንደሚቻል ያስተምረናል።

ከጥልቀቱ አናጻር፥ ሰላም፦ ውስጣዊ  ወይም ውጫዊ፣ የግል ወይም የጋራ፣ ጊዜያዊ ወይም ዘላቂ፣ መሰል ወይም እውነተኛ ተብሎ ሊመደብ ይችላል። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ሰው ከመሆኑ ፯፻ ዓመት በፊት፥ የሰላም ንጉሥ እንደሆነና፣ ለሰላሙም ማብቂያ እንደሌለው በነቢዩ በኢሳይያስ ተነግሮ  ነበር። ኢሳ. ፱፥፯

ሰላም ምንድን ነው?
የሁካታ ወይም የግርግር አለመኖር፣ ጸጥታ፣ መረጋጋት፣ ወይም ውሳጣዊ ዕረፍት፣ “ሰላም” የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ለማስተላለፍ ቢጠቅሙም፥ በሃይማኖት ለሚኖሩ ግን፥ ሰላም ከዚያ በላይ ነው። ሰላም፦
v እግዚአብሔር ለሚታመኑበት የሚያድላቸው፥ የመርካት ስጦታ ነው፤ ዘሌ. ፳፮፣ ኢሳ. ፳፮፥፫
v አማኞች፥ በመልካም ሲኖሩ የሚያፈሩት፥ የመንፈስ ፍሬ ነው፤ ኤፌ. ፭፥፳፪
v ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ፥ ሰዎች ለዘለዓለም እንዲኖሩት የሚመለስላቸው፥ የእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ የሚያኖር በረከት ነው፤ ኢሳ. ፲፩፥ ፮፣ ሮሜ ፲፬፥ ፯፣ ራዕ.

እውነተኛው ሰላም፤
እውነተኛ ሰላም የሚገኘው፥ ሰው ከኃጢአቱ በንስሐ ነጽቶ፥ ከእግዚአብሔር ጋር ሲታረቅ ብቻ ነው። (ሮሜ ፭፣ ኤፌ. ፪፥ ፲፬)። መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ የሰላም ንጉሥ፥ ስለሆነ፦
v ገና በቤተልሔም ሲወለድ፥ ሰላም በመላእክት ተሰበከ፤ ሉቃ. ፪፥ ፲፬፤
v በዓለም እየተዘዋወረ ሰላምን ሰበከና ፥ ለተከታዮቹ ሁሉ፥ በገባችሁበት፥ ሰላም ለዚህ ቤት ይሁን፤ በሉ!አላቸው፤ ማቴ ፲፥፲፪፤
v “እኔ የምሰጣችሁ ሰላም፥ ዓለም እንደሚሰጣችሁ ዓይነት ሰላም አይደለም! ብሎ ራሱ፥ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ታግሶና ጠላትን ድል ነስቶ፥ ልዩ ሰላምን ሰጠን፤ ዮሐ. ፲፬፥ ፳፯
v ከሞተና ከተነሣ በኋላ፥ በሲዖል ለነበሩ ነፍሳት ሰላምን ሰብኮ፥ ነጻ አወጣቸው፤ ፩ኛ ጴጥ.  ፫፥፲፱
v በመጨረሻም፥ በፍርሃት ተይዘውና ተደብቀው፥ በዝግ ቤት ውስጥ ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱ፥ ሰላም ለእናንተ ይሁን! አላችው። ሉቃ. ፳፬
v ዛሬም በኦርቶዶክሳዊ ሥርአተ አምልኮና ቅዳሴ ጊዜ፥ ካህኑ ሰላም ለኵልክሙ በማለት የክርስቶስን ሰላም ይሰብካል።

ውስጣዊ  v. ውጫዊ  ሰላም
ውጫዊ ሰላም ፥ የሰው ልጆች በመካከላቸውና ከአካባቢያቸው ጋር በሚያደርጉት መስተጋብር፥ በስምምነትና  በኅብረት ከኖሩ የሚፈጠር አንጻራዊ የእረፍት ስሜት ነው። 


የዚህ ዓይነቱ ሰላም፥ በብዙ  ቅድመ  ሁኔታዎች ላይ የተምሠረተ ስለሆነ፥ በተለያዩ ምክንያቶች ሊደፈርስ ይችላል። እግዚአብሔር ከሚሰጠው ሰላምም፥ በእጅጉ የተለየ ነው። ዮሐ. ፲፬ ፥፳፯።  በአብዛኛው በጦርነት፣ በድርድር፣ በስብሰባ፣ ወይም ካልሆነ፥ በአንጻራዊ የኃይል የበላይነት ይገኛል፤ በቀላሉ  ይደፈርሳል። በተለይ በክርስቲያኖች መካከል ያለው ሰላም፥ በቅድመ ሁኔታ ላይ ሲመሰረትና በቀላሉ ሲደፈርስ፥ የሰው ልጅ ኑሮ ብዙ ጉስቁልና እንዲበዛበት ከሚያደርጉ  ምክንያቶች ዋናው እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ። ፩ኛ ቆሮ. ፩፥ ፲-፲፯። “ጨው አልጫ ቢሆን፥ ግን በምን ይጣፍጣል?” ሌላውስ በምን ይጣ’ፈጣል? ማቴ.፭፥፲፫

በሌላ በኩል፥ ውስጣዊ ሰላም፥ የአንድ ሰው ከራሱ ተፈጥሮ የተነሳ፥ የነፍስና የሥጋ ባሕርያቶቹ መስማማት፥ በሃይማኖታዊ አነጋገር፥ መንፈስ በሥጋ ላይ ሲሰለጥን የሚፈጠር የመንፈስ ፍሬ ነው። ገላ. ፭፥ ፳፪። በእውነተኛው የሰው ተፈጥሮና የእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ዕቅድ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ፥ ዘላቂና እውነተኛ ነው። የሚገኘውም የራስን ተፈጥሮና የእግዚአብሔርን ሃሳብ በመረዳት ብቻ ነው። ውስጣዊ ሰላም ሲኖረን፥ በፍቅር እንመላለሳለን፤ ይቅር እንባባላለን፤ የጠራን ቅዱስ ነውና፥ እኛም ቅዱሳን እንሆናለን! 
  
ማጠቃለያ
የእግዚአብሔር ሰላም የሚገኘው፥ በወንጌሉ ቃል ለእግዚአብሔር ስንታዘዝ ብቻ ነው። ይህ ሰላም፥ ራሱ  መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ለእኛም ሰላማችን እርሱ ስለሆነና ለሚታዘዙለት የራሱን ሰላም ስለሚሰጣቸው፣ ስንታዘዝ ውስጣዊ  ሰላም ስለምናገኝ ፥ ቅ. ጳውሎስ እንዳለውም በጌታ  ደስ ይለናል።

በዚህ የምናከብረው የትንሣኤ ሰሞን፥ “ሰላም ለእናንተ  ይሁን!” የሚለው የትንሳኤው መታሰቢያ ዜናና፥ የእግዚአብሔር ሰላም፥ ለሐዋርያት ደስታን ፈጥሮላቸው ነበር። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ፥ የእግዚአብሔር ሰላም፦ ልባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቅና፣ ደስም ይላችሁ ዘንድ፥ “ሰላም ለእናንተ  ይሁን!!!”

Thursday, May 15, 2014

Resurrection/Tinsa'e ትንሣኤ


ከክርስቶስ ጋር መነሣት

“ከክርስቶስ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን።”
    ሮሜ፥ ፮፥ ፯ ፰

ስለ ትንሣኤ ሲታሰብ፥ ቀድሞ  የሚመጣው፥ የሞት ጉዳይ ነው። ሞት የማይቀር የተፈጥሮ  ሂደትና በትቂቶች ዘንድ የሚጠበቅ ክስተት ቢሆንም፥ በብዙ ሰዎች ዘንድ ግን፥ የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ እውነታ ነው። ሞት፥ በሳይንስ፥ ሕይወትን ደግፈው ያኖሩ አካላት፥ ለምሳሌ እንደ  ልብ ያሉ፥ አገልግሎት ማቆማቸውን ሲያመላክት፥ በማኅበራዊ  ሕይወት ግን፥ አንድ ወጥ የሆነ ትርጕም ያልተገኘለት፣ ለዘመናት የሃይማኖትና የፍልስፍና ጠበብቶችን ያነጋገረና፣ በማነጋገር ላይም የሚገኝ፥ የሕይወት ሌላኛው ገጽታ ነው። ሞት፥ በቅዱሱ መጽሐፍ፥ ከ፰፻ ጊዜ በላይ ተጠቅሷል። ቅዱስ ጳውሎስም በመልእክቱ፥ “ከክርስቶስ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር በሕይወት እንኖራለን።”በማለት የሚያስፈራው ሞት፥ ለመኖር ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይመክራል።  ታዲያ በዚህች አጭር ጽሑፍ የምንመለከትው፥ ስለሞት ምንነት ሳይሆን፥ ሞት ከሕይወት ጋር ያለውን ግንኙነት ይሆናል።  



የሞት አገባባዊ ትርጕም፦

በክርስትና ሃይማኖት፥ ሞት በሁለት ይከፈላል፤ የመጀመሪያው ሞት፥ ሰው[1] ከአራቱ ባሕርያተ ሥጋ የተፈጠረ በመሆኑ ዐፈር ነዉና፥ ወደ ተፈጠረበት ዐፈር የሚመለስበት የሥጋ ሞት ነው። ዘ. ፫፥ ፲፱። ሁለተኛው ሞት ደግሞ፥ ሰው ከሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ ስለተፈጠረ፥ የማትሞትና የማስበሰብስ ነፍስ አለውና፥ ከእግዚአብሔር ክብር ተለይቶ የሚኖረው፥ የስቃይ ኑሮ ነው። የመጀመሪያው ሥጋዊ ሞት፥ ሁሉም የሰው ዘር የማይቀርለት ሞት ነው፤ ሁለተኛው ሞት ግን፥ ሰዎች ከአምላካቸው ጋር የሰመረ ግንኙነት ሲኖሩ የማያስፈራቸውና፥ ሥጋዊ ኑሯቸውን ያለእግዚአብሔር በዘፈቀደ ኖረው ሲሞቱ ደግሞ፥ እጅግ በጣም የሚያስፈራ እንደሆነ፥ ቅዱስ ዮሐንስ በራእዩ አብራርቶታል። ራዕ.፳፥ ፮።

እግዚአብሔር፥ አባታችን አዳምን፦ “መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።”ብሎት ነበር። ዘፍ. ፪፥፲፯። ነገር ግን፥ አዳም ከዛፊቱ  በበላ ጊዜ ወዲያውኑ በሥጋ አልሞተም፤ ስለዚህ፥ ሞት ማለት፥ ከእግዚአብሔር ክብር ተለይቶ፥ ከዓላማ ውጭ ሁኖ መኖር ማለት እንጅ፥ በሥጋ መሞት ማለት እንዳልሆነ እንገነዘባለን። የጠፋውን ልጁን መመለስ ይጠባበቅ የነበረውም አባት ልጁ  ሲመለስ፥ “ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና፥ ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤” ያለው፥ ልጁ፥ እኛ እንደምናስበው ዓይነት ሞት ሞቶና ተቀብሮ ስለነበረ አይደለም። ሉቃ. ፲፭፥ ፳፬። ነገር ግን፥ በሥጋ ሞተው፥ በነፍስ ግን ሕያው ሆነው የሚኖሩ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፥ በሥጋ እየኖሩ፥ በመንፈስ ግን የሌሉ፣ የቁም ሙቶች እንዳሉ ለማሳየት ነው። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ፥ ሙታን የሚባሉት የተፈጠሩበትን ዓላማ የማያውቁ፣ በአዳማዊ አለመታዘዝ የሚኖሩ፣ ከፍቅር ይልቅ በጥላቻ፣ ከመገንባት ይልቅ በማፍረስ ፥ ከመፈወስ ይልቅ በማፍረስ፣ ከእውነት ይልቅ በሐሰት፣ ከወንድማማችነት ይልቅ በጠላትነት፣ ከማስማማት ይልቅ በማጣላት፣ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው።

በመንፈሳዊው ዓለም፥ ሞት የሐጢአት ውጤት ነውና፥ በአዳም አለመታዘ ምክንያት ወደ  ሰዎች መጣ፤ ሮሜ ፭፥ ፲፪። ሰዎችም፥ የሞት ተገዥዎች ሆኑ። ታዲያ ሰው ራሱም ሆነ፥ በሰው ምክንያት የተረገመችው ምድር ያበቀለው መስዋዕት፥ የሰውን ልጅ ወደ ቀደመ ክብሩ መመለስ ስላልተቻላቸው፥ ሞትን ይሽር ዘንድ፥ ክርስቶስ ወደ ዓለም ሰው ሆኖ መጣ። ‘ሰጥቶ መቀበል ይሉሃል ይሄ ነው።’ የማይሞተው አምላክ በሥጋ ሲሞትና የሰውን ባሕርይ ባሕርዩ ሲያደርግ፥ ሞት የተፈረደበት የሰው ዘር ደግሞ፥ የወረደውን የአምላክን መለኮት ባሕርዩ  አድርጎ፥ ከሞት ተነሳና በሞት ላይ እንደገና ሥልጣንን ተቀዳጀ።   

ከክርስቶስ ጋር መሞት፤
ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን፥ ክርስቶስ በሞቱ ሞትን ሽሮታል፤ የሞትን ፍርሃትና መውጊያም አስወግዶታል። ፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥ ፶፫፣ ዕብ. ፪፥ ፱። ይህ ማለት ግን፥ በሥጋ አንሞትም ማለት አይደለም፤  ነገር ግን፥ የዚህን ዓለም የሐጢአት ሥራ ስለክርስቶስ ብለን፥ ከናቅነውና ፥ ራሳችንን ለምቀኝነት፣ ለጥላቻ፣ ለአድመኝነት፣ ለዝሙትና ለመሳሰለው ክፉ ነገር፣  እንደሞተ ሰው ከቆጠርነው፥ ከክርስቶስ ጋር በእውነት ሞተናል ማለት ነው፤ ክርስቶስ በተከሰሰ ጊዜ፥ ቢናገራቸው ሊያሳምኑ የሞችሉ፥ ብዙ መልካም ቃላት ነበሩት፤ ነገር ግን ዝም አለ፤ ምራቅ ለተፋበት ሰው፥ ሊመልስለት የሚችለው፥ ብዙ ዋጋ ነበረው፤ ነገር ግን እንደ ክፋቱ አልመለሰለትም፤ ለተመጻደቁበት፥ እውነተኛነቱን የሚያሳይበት፥ ብዙ መንገድ ነበረው፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው አሳልፎ  ሰጠ  እንጅ። ፩ኛ ጴጥ. ፪፥፳፬። ስለዚህ ከክርስቶስ ጋር መሞት ማለት፥ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት አስወግደን፣ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፥ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት መሮጥ ማለት ነው። ዕብ. ፲፪፥ ፩።

ማጠቃለያ፦ ከክርስቶስ ጋር በሕይወት መኖር፤
ሞት ለክርስቲያኖች፥ እንደራሳቸው ሳይሆን፥ እንደ  እግዚአብሔር ፈቃድ ለሚኖሩት፥ ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዘለዓለማዊ ሕይወት መሸጋገሪያ ድልድይ ነው። ስለዚህም ቅዱሳን ሥጋዊ ሞትን፥ ጊዜውን ጠብቆ  እስኪመጣ ድረስ ይናፍቁታል። ቅዱስ ጳውሎስ፥ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።” ይለናል። ፊል.፩፥፳፫። ምክንያቱም፥ በሥጋዊ ሞት መሄድ፥ ከክርስቶስም ጋር ለመኖር ስለሆነ፥ ይናፈቃል፤ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ነውና፤ ክርስቶስን አምነው የሞቱ፥
1. ለዘለዓለም ከእርሱ  ጋር ይኖራሉ፤ ኢሳ.፴፭፥፲፣ ሉቃ. ፳፫፥ ፵፫
2. አጥርተው ያያሉ፤ አዋቂዎች ይሆናሉ፤ ፩ኛ. ቆሮ. ፲፫፥፲፪
3. ዕረፍትን ያገኛሉ፤ ራዕ. ፯፥፲፩፣ ፲፬፥፲፫
4. ከክርስቶስ ጋር፥ ሺህ ዓመት ይነግሣሉ። ራዕ. ፳፥፮


[1] ሰው የሚለው ሃሳብ፥ ሰብእ ከሚለው የግእዝ ቃል የተወረሰ ሲሆን፥ ትርጕሙም፥ ከሰባት ንጥረ ነገሮች/ባሕርት የተሰራ ማለት ነው፤ ሰባቱም፥ አራቱ  ባሕርያት ሥጋ፥ ሦስቱ  ደግሞ  ባሕርያተ ነፍስ ይባላሉ።